ቤተክርስቲያናችን

ቤተክርስቲያናችን እንዳትናድ አባቶቻችን አንድ እንዲሆኑና በአንድ ሲኖዶስ እንድንመራ

============================================================

ጥንተ  እምነት፡

አምልኮተ እግዚአብሄር ፡ በሳል የአስተዳደር ችሎታ፡ ፍትሃዊነት፡ ለዕምነት ጽናት ፡ በረሃና ውቅያኖስ አቆርጦ ለእምነት መሞት ፣ ከራስ ጥቅም ይልቅ ሃብትና ንብረትን ለዕግዚአብሄር የማዋል ምግባር ከጥንት በአባቶቻችን አኩሪ መሰረት የነበረን መሆኑ በቅዱስ መጽሃፍ በየቦታው ተጠቅሶ ይገኛል፡፡

·       ደገኛው የምድያም ካህን ዮቶር ያለምንም ጥቅም  ፍለጋ ታላቁን ነቢይ ሙሴን አስጠግቶ ፥ህይወቱን አትርፎ፣ ልጁን እስከመዳር መታደጉ፣ ኦሪት ዘጸዓት፡ ም፡ 2 ቁ 15፡21 ።

·       ዮቶር የሙሴ አማት የጠለቀ ያስተዳደር ችሎታ እንዳለው ፥ ሙሴ ብቻውን ሲደክም ሰዎች መርጦ ፥ኃላፊ እሰልጥኖ ፥ሃላፊነትን እንዲያካፍል መምከሩ ፡ኦሪት ዘጸአት ም፡ 18 ቁ 18፡24።

·       ኢትዮጵያዊው የንጉስ ባለሟል አቤሜሌክ ስልጣኑን ወይም ህይወቱን ሊያሳጣው የሚችል ቆራጥ አቋም ወስዶ ፥የነቢዩ ኤርምያስን ህይወት ከሞት ማዳኑ ፡ትንቢተ ኤርምያስ ምዕራፍ 38 ቁ 7፡13።

·        ንግስተ ሳባ እግዚአብሔር ለሰለሞን  የሰጠውን ዕውቀት በማድነቅ በዚያን ዘመን ወደ ቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ስትሄድ የወሰደችውን የስጦታ ዓይነት ብዛትና የተሰጣት ክብር፡መጽሃፈ  ነገስት  ቀዳማዊ  ምዕራፍ  10  ቁ  1፡13።

በዘመነ ሀዲስ፡

·       ገና አውሮፓውያንና ሌላው ዓለም ስለክርስቶስ ምንም ባላወቀበት ኢትዮጵያዊው ጃንደርባ  ለመሳለም ኢየሩሳሌም ሄዶ ሳለ፥ የነቢዩ ኢሳይያስን መጽሃፍ ሲያነብ መንፈስ ዕምነቱን ተመልክቶ፥ ሃዋርያው ፊሊጶስን በመላክ ገና በ34 ዓመተ ምህረት የክርስቶስን ማዳን አምኖ ፥ተጠምቆ ወደ ሃገሩ ክርስትናን ይዞ መመለሱ፡የሐዋርያት ሥራ ም፡ 8 ቁ 26፡39

·       በ325 ዓመተ ምህረት በኒቅያ ንጉስ ቁስጠንጢኖስ በሰበሰባቸው  318 ሊቃውንት የጸደቀውን ትክክለኛ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት በ328 ዓም በፍሬምናጦስ/አባ ሰላማ አማካይነት ከግብጽ ቅዱስ ማርቆስ መንበር በይፋ በመቀበል ጥንታዊ  ከሚባሉት አብያተ ክርስቲያናት አንዷ ስትሆን ታላቅ እምነት ያላቸው አባቶች ፣ ምዕመናንና ፣ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ፡አፍርታለች።  /የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤት ክርስቲያን ሃይማኖት እምነትና ሥርዓት/ አቶ በእደ ማርያም እጅጉ ረታ 2004 ዓ ም

·       ዛሬ በቅድስት ሃገር ኢየሩሳሌም ፥ጌታ በተወለደበት በቤተልሄም፥ በተሰቀለበት ጎልጎታ፥ ሙት ባስነሳበት አልዓዛር፥ 40 ቀን ጾሞ በጸለየበት ቆርንቶስ እጠገብ በኢያሪኮ ባጠቃላይ 7 ገዳማት ይዞ መገኘት፣

·       በአክሱም የሙሴ ጽላት፡ በግሼን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግማደ መስቀል መገኘት፣

·       ዓለምን የሚያስገርመው የቅዱስ ላሊበላ ቤተክርስቲያናት፡ የበርካታ ቅዱሳን፡የያሬድ ማህሌት፡ የቅዳሴ ስርዓት፡ዝማሬ፡ መንፈሳዊ መጻህፍቶች፣ ታሪክና ቅርሷ ይመሰክራል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከተመሰረተችበት ጀምሮ በአማኞቿ  ጽናት በሃገር ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ስትታወቅ፣ በየጊዜው ዕድገትዋን የሚጎትቱ መሰረቷን ለማናጋት የሚችሉ ችግሮችም አልጠፉም።

ቤተክርስቲያናችን  ትላንት ያሳለፈቻቸው ፣ ዛሬ የምትገኝበትና  የነገ  አስፈሪ  ችግሮች

1.     በዮዲት ፣ በግራኝ መሐመድና በፋሽስት ኢጣልያ  ወረራዎች አያሌ አብያተ ክርስቲያናትና መጻህፍት መቃጠል፣ መዘረፍ፣ ካህናትና ክርስቲያኖች መገደል፣

2.     ለ1621 ዓመታት ማለትም እስከ 1951 ዓም ድረስ የራስዋ ፓትርያርክ ሳይኖራት ቋንቋዋንና ባህልዋን በማያውቁ የግብጽ ጳጳሳት መመራትና ለዚያም ትከፍለው የነበረው ክፍተኛ ወጭ፣

3.    ከብዙ ጥረት በሁዋላ የራሷን የመጀመርያ  ፓትርያርክ መምረጥ ጀምራ ገና በዕድገት ጎዳና ለመራመድ ዳዴ እንደጀመረች በ1966 ሥልጣን በያዘው ወታደራዊ ኮሚኒስት የደርግ መንግስት ቤተክርስቲያኗ  ሃብትዋ  መወረሱና ለችግር መዳረግ፣

4.    በ1951 የተሾሙት የመጀመሪያው ፓትርያርክ ሲያርፉ በ1963 የተሾሙት ሁለተኛውን ፓትርያርክ ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስን ደርግ በ1968 ዓም አስሮ እርሳቸው  በህይወት እያሉ ሌላ ፓትርያርክ ሾሞ ፣ ከእስርና እንግልት በሁዋላ ያለፍርድ መግደሉ፡ሌሎችም ጳጳሳት፡ ካህናት፡ ምዕመናን  ተሰደው የቤተክርስቲያንዋን አስተዳደር መሰረት  መናጋት፣ እንዲሁም በነበረው በኮሚኒስት መንፈስ ክርስትናን ማዳከም፣

5.    በ1983 ሌላ መንግስት ሲቀየር፡ ከደርግ በለመደው የነበሩት ፓትርያርክ ብጹዕ አቡነ መርቆርዮስ  በህይወት እያሉ ብጹዕ አቡነ ጳዎሎስን ፓትርያርክ መሾሙ ፣በአቡነ መርቆርዮስ የሚመራ ስደተኛ ህጋዊ  ሲኖዶስ ተቋቋሞ ሲኖዶሱ በሁለት መከፈሉ፣

6.    እስልምና ሲጀመር በ7ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያዎቹን እስልምና እምነት ስደተኞች ተቀብለው በመከባበር ለዘመናት ተስማምቶ አብሮ የመኖር ሁኔታ ባህላችን ጠፍቶ መላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያን  ቤተክርስቲያን ገንብተው በነጻ አምላካን ማመስገን ሲችሉ ዛሪ  በተወለዱበት እናት ሃገራቸው ውስጥ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ቤተ ክርስቲያናት በየቦታው በእሳት እየጋዩና  እየተዘጉ ፡ ካህናቶች፡ዲያቆናትና  ምዕመና  እየታረዱ የተረፉት እንዲሰደዱ  ማምለክ አለመቻል እየበዛ መሄድ፡

7.    ጥንት ለትምህርት ይላኩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ትምህርታቸውን እንደጨረሱ ቢለመኑ እንኩዋን በውጭ ሳይቀሩ ወደሃገራቸው እምቢ ብለው ይመለሱ የነበረበው ሂደት፣ በሃገር ተከብሮ በሰላም የመስራትና ፡ የመኖር ዋስትናና ፡ የሃገር ፍቅር ፡ ተንዶ  ችግርና ረሃብ በመንገሱ፣ ላለፉት 40 ዓመታት ኢትዮጵያውያን በመላው ዓለም በመሰደዳቸው ካላቸው የዕምነት ፍቅር በየቦታው በሚከፈቱ ቤተ ክርስቲያናት ጠብና ክስ መንገስ

 ኢትዮጵያዊ ባለበት ቦታ ሁሉ ቤተክርስቲያን፣ የሃገር ልብስ፣ እንጀራና ወጥ የሚገኝበት ያበሻ ምግብ ቤት መጀመርና ማደግ የሚደገፍ ነው። ሁሉም ነገር ለበጎ እንደሆነ ሁሉ ለሁለት ሺሀ ዓመታት በመላው ዓለም የተበተኑ እስረኤላውያን በሄዱበት ሁሉ በንግድ ፡በትምህርት በመጎልበት ፣ ዕውቀትና ንብረት በማፍራት ከምድረ ገጽ ጠፍታ የነበረችውን እስራኤል እንደገና እንደወለዷት ሁሉ፣ የኢትዮጵያውያንም በመላው ዓለም መበተንና ማደግ ከስታ የጠቋቆረችውን ኢትዮጵያ እንድታብብና መልካም ፍሬ እንድታፈራ ያደርጓታል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም ላይ ያንዣበቡት ችግሮች በሰላም ከተፈቱ የወደፊት ዕጣዋ ያማረ እንደሚሆን መገመት ነቢይ መሆንን አይጠይቅም። እግዚአብሄር ከኛ የበለጠ የሚያውቅና የወደደውን እንደሚያደርግ ሁሉ ሁኔታዎችን ስንመለከት፦ 

·       ዛሬ  በአብዛኛው የምዕራቡ ዓለም ቤተ ክርስቲያናት  እየተዘጉ፡ አማኝና አምልኮተ እግዚአብሄር የሚፈጽም  በመጥፋቱ፡ ወደ ንግድ ቤት እየተለወጡ  ባለበት ዘመን ብዙዎቹ ቤተክርስቲያናት በኢትዮ ጵያ ኦርቶዶክስ ዓማኞች  እየተገዙ ፡አዲሶችም  እየተገነቡ ናቸው።

·       በልዩ ስርዓት የሚቀርበው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ  ጸሎት በመላው ዓለም እየፈሰሰ  ፣ ታቦተ ሕግ በፖሊስ ሞተር እየታጀበ በታላላቅ የአሜሪካ፡ አውሮፓና  ካናዳ  ከተሞች ጥምቀት  እየተከበረ ፣ ይገኛል።

·       ዓለም ትክክለኛው አምላክ ለሙሴና አሮን ባዘዘው ክብር የተላበሰ እምልኮትን በማየታቸው ብዙዎች ይህ ነው አምልኮተ እግዚአብሄር እያሉ እየተጠመቁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታይ እየሆኑ ናቸው።

·       ሃብትና ገንዘብ ይዞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስን ቤተክርስቲያን እናስፋፋ ተብሎ መንግስት ወይም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኝ ቢጠይቅ አንድም ቤተ ክርስቲያን ተፈቅዶ ለመስራት አይቻልም ነበር ። አሁን ግን በንቂያው የኦርቶዶክስ የአምልኮት ስርዓት መሰረት የተመሰረተችውና ልዩ የራስዋ የቅዳሴ ስርዓተ አገልግሎት ለመላው ዓለም እንዲታወቅ እምላክ የፈቀደው ነው ለማለት በሚያስችል ግንዛቤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ቅዳሴ በሃያልዋ አሜሪካ ባሉ በመላው 50 ስቴቶች ከተሞችና፡ መላው ዓለም  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሰ ቤተክርስትያን  ግንባታ እያበበ ነው። 

 

 ይህ ቀላል ይመስላል ግን እጅግ ልዩ አጋጣሚ ነው እንኩዋንስ ለቤተክርስቲያናችን ለሃገራችንም ትንሳኤ ቁልፍ  የሆናል።ባንድ በኩል የቤተ ክርስትያናችን በመላው ዓለም መከፈት ሲያስደስት ከእርሱ ጋር ግን ፈጽሞ ያልተጠበቀ ለቤተክርስቲያናችን ህልውና  ፈታኝ የሆነ ችግርን አስከትሏል።

1.     የሚከፈቱት ቤተክርስቲያናት አስተዳደር በኢትዮጵያ ሲኖዶስ ፣ በስደተኛ ሲኖዶስ ፣ ሁለቱንም በማይቀበሉ ገለልተኛ በሚል በሶስት ዘርፍ  ተከፍለው  በዘርና  በጎሳ ሳይለያዩ  ባንዲት ቤተክርስቲያን  የኖሩት  ምእመናን እንደጠላት ያለጠባቂ እንዳሻቸው ቀኖና መጣስ፡

2.    ሲጀመሩ ከዕምነት ፍቅር አንጻር ደንብና  ህግ ግምት ገብቶ ደንብ ሳይዘጋጅ  ምንም አይደለም እየተባሉ የተጀመሩ ቤተክርስቲያናት መደርጀት ሲጀምሩ በሚፈጠሩ መንፈሳዊነት የጎደለው የካህናትና ምዕመናን አመለካከትና እለመግባባት በየቦታው ባሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያኖች  ሁኔታዎ ች ሲታዩ ፡

·        ለእምነት ማስፋፋት ሳይሆን ከሃገር ባስወጣን  እልህ ፡ ለመቻቻል በመጣር ፋንታ  ተለይቶ ቤተክርስቲያን  እንደሱቅ  በየቦታው መክፈት፣

·       አመራር እንዲስተካከል የሚነሱ ችግሮችን እንደመንፈሳዊ  በሰላም  በመጨረስ ፋንታ በየፍርድ ቤት ተካሶ ከምዕመናን የተሰበሰበ ገንዘብን ስንት ችግር በሃገርና ባሉበት ሁሉ ያለውን ዘንግቶ ለቤተ ክርስቲያንዋ እድገት እንዳይውል ለጠበቃ ሲሳይ መዳረግ፣

·       በየስርቻው እንዴት ተከፍተው እንዴት እንደሚዘጉ የማይታወቁ  ምእመናን የሚወዷቸውን ታቦት ስም በመያዝ በየስርቻው የእገሌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እዚህ ተከፈተ ምእመናን ካላቸው የታቦት ፍቅር ይሄዳሉ፣ ወዲያው ቤተክርስቲያን እንግዛ ገንዘብ ስብሰባ፣ ወዲያው ተካሰው ተዘጋ የሚለው በመላው ዓለም ባሉ ቤተክርስቲያኖች ስርዓትንና ቀኖና በመሸርሸር ማዳከም፣

·       እንኩዋንስ ክርስቲያን ተብሎ በክርስቶስ ያመነ ቀርቶ ከተራ ዓለማዊ የማይሰማ ህገ ወጥ የስድብ ናዳ፡ የሚሰማባት፡ቲያትረኞች በየመድረኩ የሚቀልዱባት፡ ሰው ከአምላኩጋር በፍቅር ለመነጋገር፡ ሰላም ለማግኘት የሚሄድባትን ቦታ በአካባቢው ላለመድረስ ዕርም በቤቴ እጸልያለሁ እያሉ መቅረትና የኛ ቤተክርስቲያን ማፈርያ እየሆነች መምጣትዋ፣

·        በውጭ ተወልደው ቤተክርስቲያን በመምጣት ያሉ ልጆች ትላንት አባቶች ብለው ያከበሯቸውን፥ በማግስቱ በሚያዩት ጸብ ፈጽመው እየተደናገሩ ከቤተክርስቲያንዋ እንዲርቁና ፥በየስርቻው ተከፍተው ተረካቢ አልባ እየሆኑ እንደሚሸጡና  እንደሚዘጉ በሚያደርግ የፈተና ጉዞ ውስጥ ናት።                                                                                                                                                                                                                                                               

 በኢትዮጵያ ውስጥ ሁኔታው አመች ባለመሆኑ ገለልተኛ ፣ የአሜሪካ፣ ህጋዊ ሲኖዶስ የሚባል አልተጀመረም እንጂ እ በዚህ ቀዳዳ ገብቶ ህዝብን ለመከፋፈል እንደፈለገ ማቋቋም ይቻላል ቢባል ይህ የተጀመረ የመከፋፈል መንፈስ በኢትዮጵየ ውስጥ ሊያስከትል የሚችለውን እልቂት፣ በ1966 ከውጭ ተከፋፍለው በመጡ የፖለቲካ ድርጅቶች ዙሪያ ህዝቡ እንዲሰለፍና ሲያስቡት እንኩዋን የሚዘገንን የምርጥ ዜጎች እልቂት ፣ ሃገራችን ፊትዋን ወደኋላ አዙራ በችግር ፣ በበሽታ፣ በረሃብ ፣ አንድነት ጠፍቶ፣ በዘርና በጎሳ የተበተባት በሽታ ሳይድን እጅግ አስከፊ ወደ ሆነ የሃይማኖት ብጥብጥ የሚያመራና ቤተክርስቲያናችንን የሚያዳክም የተዳፈነ ፍም ቀስ በቀስ ገብቶ ቤተክርስቲያናችንን ማፍረሱ አይቀሬ ይሆናል።

መፍትሔው ምንድነው? ምዕመናን ምን እናድርግ?? 

ከሃዋርያው ጴጥሮስ ጀምሮ ለ300 ዓመታት ንጉስ ቁስጠንጢኖስ ክርስትናን ሕጋዊ  ሃይማኖት ነው ብሎ እስካወጀበት ጊዜ ድረስ ክርስቲያኖች በፈተናቸው ሁሉ አንድ ነበሩ። ልክ ነጻንታቸውን ሲያገኙ እርስ በርሳቸው የፈጠሩት ጠብና ጥል በጦርነት አሽንፎ አንድ ያደረገው የሮማን ግዛቱን የሚበታትንበት ስለሆነበት፥  የኒቅያን ጉባኤ በመጥራት 318 የሚሆኑ የዓለም አብያተ ክርስቲያኖች ጳጳሳትን ሰብስቦ ጉባኤውን በመምራት ክርስትናን መልክ ለማስያዝና  የኒቅያ ክሪድ የሚባለውን መመሪያ ለማስጸደቅ ችሎ እስከአሁንም የክርስትና ደርዝ ያለው የሃይማኖት እምነት መሰረት ጥሎ ሁሉም የሚመራበት አርጓል።

 የቤተክርስቲያናችን አባቶች መለያየት ብዙሃኑን የሃይማኖት አባቶች ጳጳሳት፡ ካህናት፡ዲያቆናት፡ መነኮሳት፡ መምህራን ፡ ምዕመናን ፡በጓዳ እያለቀስን እያወራን በመቀመጣችን ዛሬ የኢትዮ ጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የደረሰችበትንና  ክብሯ እያቆለቆለ፡መቀለጃና፡ማፈሪያ ድርጊቶች እየተፈጸሙ ነው። ክርስትና የጌታን ፈለግ ተከትሎ 120 ሆነው የጀመሩት ሲያድግ ፣ሰብሳቢ፣ አንድ ዓይነት ዕምነት ለማኪያሄድ የሚያስችል መሪ የግድ በመሆኑ የአካባቢ፡ የሃገር፡የዓለም አብያተ ካውንስል ተቃቁሞ ክርስቲያኖች የሚመሩበት እንድ ዓይነት የዕምነት መመሪያ ወጥቶ ሁሉም ያንን ተከትሎ በአንድ የክርስትና ቀኖና ይመራል።የኢትዮጵያ ሲኖዶስም በተቋቋመበት ዓላማና ተግባር መሰረት ክርስትናችን እንዳይዛባ በአንድ ዓይነት ህግ ለመምራት ባለመቻሉ ህልውናዋን በየመልኩ የሚፈትናት የካንሰር ሰንኮፍ መላ ሰውነቷን ወርሮ እየበላት ስለሆነ አፋጣኝ መፍትሄ ከሌለ፡ ከብዙ ጠላቶቿ ጋር አብሮ ሊገድላት ይችላል።ምክንያቱም፦

·       የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ወደሚሞቱበት ያለፍርሃት ሞተው ያቆዩንን ክርስትና ዛሬ የቤተክርስቲያናችንን ጥፋት ዓይቶ  እንደ ንጉስ ቁስጠንጢኖስ የሚገስጽ  መሪ የለም፡፡

·       ዳኝነትም ሆነ ሽምግልና አንድ ወገንን ማስኮረፉ አይቀርም። ነገር ግን ጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ለሃዋርያው ጴጥሮስ በጎቼን ጠብቅ ብሎ የሰጠውን ቁልፍና አንተ ዓለት ነህ በዚህ ቤተክርስቲያኔን ትመሰርታለህ ብሎ፥ ጌታው ሞቶ የሰጠውን ክርስትና ቃል አክብሮ በሮማ አደባባይ ተሰቅሎ የመሰረታትንና ተከታዮቹም  ለ300 ዓመት ሞተው የተመሰረተችውን ቤተ ክርስቲያናችንን አንድ አድርገው እንዲመሩና  መንጋቸውን ለመጠበቅ የተመረጡ ብጹዓን አባቶቻንን  ሌሊት በጸሎት  ሲነቁ  እየሆነ ያለውን  ሰደድ  እሳት  አይተው በቆራጥነት  እስከሞትም  ቢሆን ቤተክርስቲያናችንን አንድ ለማድረግ ካልተነሱ እነሱን ለማስታረቅ ማንም አይችልም።

 

o   ሺህ ገዳይ ቢሆንም ሳዖል በጊዜው ዳዊት የኛ ንጉስ ዕልፍ ገዳይ ነው” መጽሃፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ ምዕራፍ 18፡ቁ 7፡8 ብለው ዳዊትን ሲያሞገሱ ንጉስ ሳዖል  ሰለሰማ ዕልፍ በምትለዋ ቃል ሊገድለው ጦር ይዞ የመጣውን ንጉስ ሳዖልን ፡ ባለበት በዋሻው በእጁ ላይ መጥቶለት  ሊገድለው ሲችል ምህረት አርጎ ፣ ልዑል ጌታዬ ብሎ ለምህረት ለፍቅር እንደቆመ ፡መጽሃፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ ምዕራፍ 24 ቂጥር 2 እስከ 22። እናንተም በሃገርና በውጭ ያላችሁ ብጹዓን  አባቶቻችን ምድራዊ  ሃይልን  ሳትፈሩ  እራሳችሁ  የአንድነት  መረዋ ደወል ብታሰሙ 40 ሚሊዮን ምዕመን ከናንተ ጋር ቆሞ ቅዱሳን ብሎ ለዘለዓለም የሚዘክራችሁ ይሆናልና ፣ እናንተው አባቶቻችንን  ሃሳቡን  በመደገፍ በመነኩሴ መድረክ የሰላም መልእከት እንድታሰሙን  መላ ምእመናን በዚህ ጌታ ጾሞ ፍቅሩን ባሳየበት፣ ጥላቻንና ቂምን ቀብሮ የፍቅር ቀንዲል ሰጥቶ  እንድታገለግሉት  በሰጣችሁ  ሃላፊነትና አባትነት ዘመናችሁ ሳያልቅ አንድ  የምትወዷት ቤተ ክርስቲያን  አንድ እንድታደርጉ በአክብሮት የምእመናን ድምጽ በማሰማት፥ እንማጸናለን፡

 

በዚሁ አንጻር ደግሞ

§  አባቶቻችንን ወደሰላም በመምጣት ቤተ ክርስቲያናችን ወደ ሰላም እንድትመለስ አባቶች ወደ አንድነት እንዲመጡ ብዙ አዋቂ የሆናችሁ ጳጳሳት፡ካህናት፡ ሰባክያን፡ የቤተክርስቲያን አባቶች ፡ ምዕመናን ፣ጨዋነት የተመላበት የሰላም ሃሳብን በመነኩሴ መድረክ በመጠቀም ጥረታችሁን ባለማሰለስ እንድትቀጥሉ፣

§  40 ሚሊዮን እንሆናለን ተብለን የምንገመተው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ  ተዋህዶ  ምዕመናን የስም አማኝ በመሆን ቤተክርስቲያናችን ስትጠፋ እየተመለከትን በሁዋላ ስናጣት ምን ያህል ለራሳችንና ለልጆቻችን፡ ለማንነታችን መለያ በማጣት የሚደርስብንን ውርደት ተገንዝበን በምንችለው ሁሉ በገንዘብ ወይም፡በዕውቀት ወይም በጉልበት ወይም በሃሳብ ድርሻ ብናበረክት 40 ሚሊዮን የሚለካ ሃይል ይኖራል ማለት ነው። 

§   ሁላችንም በአንድ በቁርጠኝነት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰጠን የፍቅር መንፈስ በመቆም ቤተክርስቲያናችን መንግስት በተቀየረ ቁጥር በየጊዜው የምትፈራርስ እንዳትሆን የቤተክርስቲያናችንን ልእልና ለማስከበር እንድ ላይ እንድንቆምና ቤተክርስትያናችን በየትም አገር እንደካቶሊክ ከአንድ ቢለዮን በላይ በተለያዩ  አገሮች ያሉ አማኞች ሁሉ ደንባቸውን ጠብቀው በየስርቻው ሳይከፋፈሉ እንደሚተዳደሩ፡ የኛም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በመከፋፈል እንዳትዳከም በአንድ ስርዓት እንድትመራ ለማድረግ ይረዳል በማለት ይህን የመነኩሴ ድህረ www.menekuse.org የማንም የግል ሳይሆን  ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች መንፈሳዊ  መድረክ እንዲሆን የተዘጋጀ በመሆኑ ሁላችንም በመድረኩ መንፈሳዊና  ሰላማዊ ውይይት በማድረግ  መፍትሄ እድናመጣ በትህትና እንጠይቃለን። 

  የቤተክርስቲያንትዋን ህልውና ፈተኝ የመለያየት ክስተት እንዲወገድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  በጎልጎታ ያፈሰሰውን ደም ፡ እነቅዱስ ጴጥሮስ በሮም አደባባይ የከፈሉትን መስዋዕትነትና ሌሎች ክርስቲያኖች ከ300 ዓመት በላይ የሞቱበትን ክርስቲያናዊ ዓርዓያነት በመውሰድ ሁሉም አባቶች በህይወት እያሉ ወደሰላም እንዲመጡ ሁላችንም የድርሻችንን እንድናደርግ የፍቅር ባለቤት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃድ ፡ የአማላጅ እናታችን የድንግል ማርያም አማላጅነት፡ የቅዱሳን መላዕክት ተራዳኢነት፡ የሰማዕታትና ፡ቅዱሳን ጸሎት ከኛ ጋር  እንዲሆን በማሳሰብ፣ ይህ የመነኩሴ ድህረ ገጽ www.menekuse.org

በገዳም የተሰየመው መነኮሳት የሚኖሩበት ገዳም የጸሎት የሰላም ቦታ እንደመሆኑ በመነኩሴ ድህረ ገጽም ሰላም በሰፈነበት መንፈስ በመከባበር ፣ ቤተክርስቲያናችንን አንድ በማድረግ የሚፈራርሱት ቤተክርስቲያኖቻችን እንዲገነቡ፣ እምነታችን ሳይዳከም እየተስፋፋ ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ፣ መንፈሳዊ ተግባር እንዲያድግ፣ ደረጃዋ  ከመሰል አብያተ ክርስቲያን እኩል እንዲሆን በመሆኑ፣ ዘለፋ ወይም ስድብ በመላክ የአምባጓሮ መድረክ እንዳይሆን ፣ ሰላማዊ የውይይት ሃሳቦች ብቻ ማቅረቢያና የትልቅ ተግባር መትለሚያ እንዲሆን  ሁሉም እንዲሳተፍና እንዲተባበር  የመነኩሴ ድህረ ገጽ  አዘጋጆች በታላቅ መንፈሳዊ ትህትና እናሳስባለን።

abilify

Leave a comment

Comments

  • No comments found